ብርሃን ባንክ በ2024/25 የሒሳብ ዓመት በአንድ አክሲዮን የ54.7% ትርፍ አስገኘ!

ብርሃን ባንክ አ.ማ. 16ተኛውን መደበኛ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ጥቅምት 18 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሚሊኒየም አዳራሽ አካሄዷል። በጉባዔው ላይ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኢሊጎ ለገሰ እ.ኤ.አ. ሰኔ 30 ቀን 2025 የተጠናቀቀውን የባንኩን ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለባለአክሲዮኖች አቅርበዋል። የቦርድ ሰብሳቢው በሪፖርታቸው፣ ባንኩ በዓለም አቀፍ እና በአገር አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ የተለያዩ ኩነቶች ቢኖሩም በበጀት ዓመቱ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል።
የቦርድ ሰብሳቢው በበጀት ዓመቱ በዓለም እና በአገር አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ የተለያዩ ኩነቶችን ባንኮች ማስተናገዳቸውን የገለጹ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለመጀመሪያ ጊዜ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ እንዲገቡ የሚፈቅደውን መመሪያ ማውጣቱ በዋናነት የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል። ይህ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ከፍተኛ የካፒታል ፍሰትን ወደ አገር ውስጥ የሚያመጣ፣ የገበያ ውድድርን እና የአገልግሎት አሰጣጥን የሚያሳድግ፣ የፋይናንስ አገልግሎትን አካታች እንዲሆን የሚያግዝ ሲሆን፤ በተጨማሪም ጊዜውን የዋጁ የባንክ ቴክኖሎጂዎችን ለአገሪቱ ገበያ ያስተዋውቃል ተብሎ የሚጠበቅ እንደሆነ ያነሱ ሲሆን በዚህም ረገድ ብርሃን ባንክ አቅሙን አዳብሮ ዝግጁ ሆኖ ለመገኘት ጠንክሮ በመሰራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አቶ ኢሊጎ ባንኩ የ 2024/25 በጀት ዓመቱን ሲያጠናቅቅ ከግብር በፊት ብር 2.5 ቢሊዮን ትርፍ ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀው ይህ ውጤት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ66.5 በመቶ ወይም የብር 1 ቢሊዮን ብልጫ እንዳለው߹ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ ካለፈው ዓመት የተቀማጭ ሒሳብ መጠን ጋር ሲነጻጸር የብር 7.6 ቢሊዮን ጭማሪ ወይም የ20.6 በመቶ እድገት ማሳየቱን߹ ጠቅላላ የብድር መጠን ብር 35.97 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን በዚህም የ16.7 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን߹ የውጭ ምንዛሪ የማሰባሰብ ስራውን ከዚህ ቀደም ከነበሩት ጊዜያት በላቀ ሁኔታ የ 40 በመቶ እድገት በማስመዝገብ የላቀ አፈፃፀም ማሳየቱን ገልጸዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የባንኩ አጠቃላይ ሀብት ብር 58.9 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ይኽም ባለፈው ዓመት ተመዝግቦ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር የ28.1 በመቶ እድገት አሳይቷል። የባንኩ አጠቃላይ ካፒታል ብር 8.5 ቢሊዮን በመድረስ ከባለፈው በጀት ዓመት የ20 በመቶ እድገት ባንኩ ማሳካቱን የገለጹ ሲሆን የተከፈል ካፒታሉን በተመለተ ደግሞ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተቀመጠውን አንድ ባንክ ሊያሟላ የሚገባውን አነስተኛ የካፒታል መጠን ከብር 5 ቢሊዮን በላይ ባንኩ ያሟላ መሆኑን ገልጸዋል። ይህም በመሆኑ ብርሃን ባንክ እ.ኤ.አ. ሰኔ 30 ቀን 2025 በአንድ አክሲዮን የ54.7 በመቶ ትርፍ በማስገኘት የበጀት ዓመቱን በአመርቂ ስኬት ማጠናቀቅ መቻሉን አቶ ኢሊጎ አስረድተዋል።
በተጨማሪም ባንኩ የሦስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ሙሉ ትግበራ መገባቱን የጠቀሱ ሲሆን በዚህም ምክንያት ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የደንበኞቹን ፍላጎት ለማርካትና አገልግሎት አሰጣጡን ለማላቅ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና የኮር-ባንኪንግ ሲስተም ማሻሻያ ስራዎች ተጠናቀው ወደ ሙሉ ትግበራ መገባቱ በዋናነት ይጠቀሳሉ።
በመጨረሻም ቦርዱ በቀጣይ በጀት ዓመት የባንኩን ካፒታል ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ፣ የተሻሻለ የደንበኛ አገልግሎት ለመስጠት የሚረዱ ስትራቴጂዎችን በተጠናከረ ሁኔታ መተግበር፣ የሽግግር ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታን በተያዘለት እቅድ ማጠናቀቅ እና የዲጂታል ባንኪንግ ቴክኖሎጂዎችንና ፈጠራዎችን ማስፋፋት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሚሆኑ ገልጸዋል።