ብርሃን ባንክ የብር 45.0 ቢሊዮን ሃብት አስመዘገበ

ህዳር 20 ቀን 2016 .

ብርሃን ባንክ የብር 45.0 ቢሊዮን ሃብት አስመዘገበ

ብርሃን ባንክ 14ኛ መደበኛ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ሐሙስ ህዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ አካሂዷል፡፡ በጉባኤው ላይ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ጉማቸው ኩሴ እ.ኤ.አ. ሰኔ 30 ቀን 2023 የተጠናቀቀውን የባንኩን ዓመታዊ የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለባለአክሲዮኖች አቅርበዋል፡፡

አቶ ጉማቸው እ.ኤ.አ. የ2022/23 በጀት ዓመት በአለማችን የተከሰተው የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ከፍተኛ ኢኮኖሚ ያላቸው ሃገራት ፖለቲካዊ ውጥረት ጋር ተዳምሮ በዓለም ገበያ ላይ ጫና ማሳደሩ፣ እንዲሁም በአገራችን ተከስቶ የነበረው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በባንክ ኢንዱስትሪው ላይ ያሳደረውን ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳሳደረ አብራርተዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ባንኩ እየተከሰቱ ያሉትን ሁነቶች በቅርበት በመከታተልና በመረዳት አዳዲስ ስልታዊ አቅጣጫዎችንና ተቋማዊ አደረጃጀቶችን በመፍጠር እራሱን ይበልጥ በማጠናከር ላይ እንደሚገኝና ባንኩ ሶስተኛውን የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድና ተቋማዊ መዋቅር ዝግጅት አጠናቅቆ ወደ ትግበራ መግባቱን ገልጸዋል። ከዚህም አኳያ የተበላሸ ብድር ክምችትን ለመቀነስም የተሰራው ሥራ እንዲሁም ትርፋማነትን ማሻሻል ባንኩ በበጀት ዓመቱ ካከናወናቸው ተግባራት መካከል በዋናነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን በሪፓርታቸው ላይ አመላክተዋል።

በሌላ በኩል አቶ ጉማቸው የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ካለፈው በጀት ዓመት የ29.8 በመቶ ጭማሪ በማስመዝገብ ብር 33.8 ቢሊዮን መድረሱንና የብድር ክምችትም ብር 28.9 ቢሊዮን መድረሱን ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ24.4 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን ግልጸዋል። በተጨማሪም ባንኩ 146.9 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ መሰብሰብ መቻሉንና ይህም ካለፈው የበጀት ዓመት የ 14.3 በመቶ ብልጫ እንዳስመዘገበ አብራርተዋል። በተመሳሳይ የደንበኞች ቁጥር የ 26.4 በመቶ እድገት በማስመዝገብ ከ 2 ሚሊዮን በላይ መድረሱን ገልጸዋል። በተጨማሪም ብርሃን ባንክ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ከታክስ በፊት ብር 605.2 ሚሊዮን ትርፍ ማስመዘብ የቻለ መሆኑን ገልጸው ይህም ካለፈው የበጀት ዓመት ትርፍ ጋር ሲነጻጸር የ3.7 በመቶ እድገት ማሳየቱን አብራርተዋል። የባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያሳየው የባንኩ አጠቃላይ ሃብት ብር 45 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በ 36.2 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። በተመሳሳይ የባንኩ አጠቃላይ ካፒታል 12.7 በመቶ እድገት በማስመዝገብ ብር 4.5 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ደግሞ በ6.1 በመቶ በማደግ ብር 3.4 ቢሊዮን መድረሱን ሪፖርቱ ያሳያል።

በሌላ በኩል በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ያለውን የገበያ ውድድርን መሰረት በማድረግና የደንበኞች አገልግሎቱን በመላ ሃገሪቱ ለማስፋፋት ባንኩ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች 40 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት የቅርንጫፍ ስርጭቱን ወደ 366 አሳድጓል። በተጨማሪም ባንኩ የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማርካት ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ የተለያዩ የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎቶችን በማስፋፋት ላይ እንደሚገኝም ተገጿል።

ብርሃን ባንክ  በአዲስ አበባ በተለምዶ ሰንጋተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከመንግስት በተረከበው 5400 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ ላይ ለሚያስገነባው የዋና መስሪያ ቤት ሕንፃ የስነ-ህንፃ ዲዛይን ውድድርና መረጣ ሂደት በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቁንና በተመሳሳይ በወላይታ ሶዶ ከተማ ለሚያስገነባው ሕንፃ የዲዛይን መረጣውን በበጀት ዓመቱ በማከናወን የውድድሩ አሸናፊዎችም እ.ኤ.አ. ግንቦት 10 ቀን 2023 እና ሰኔ 6 ቀን 2023 በቅደም ተከተላቸው ይፋ መደረጋቸውን የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢው ገልጸዋል።

በመጨረሻም አቶ ጉማቸው ለባንኩ ባለአክሲዮኖች፥ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፥ ለደንበኞች፥ ለባንኩ አመራርና ሠራተኞች በሙሉ ባንኩ ላስመዘገበው ስኬት ላደረጉት አስተዋፅኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ለተጨማሪ መረጃ በ 011 6 507707 ወይም 0116 185712 ይደው