ብርሃን ባንክ የ13ኛ መደበኛ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ አካሄደ

ብርሃን ባንክ 13ኛ መደበኛ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ሐሙስ ጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ አካሂዷል፡፡ በጉባኤው ላይ የባንኩ ዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ጉማቸው ኩሴ እ.ኤ.አ ሰኔ 30 ቀን 2022 የተጠናቀቀውን የባንኩን ዓመታዊ የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለባለአክሲዮኖች አቅርበዋል፡፡ አቶ ጉማቸው ኩሴ እንደገለፁት እ.ኤ.አ ሰኔ 30 ቀን 2022 የተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ባንኩ የተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎችን ያሳለፈበትና የተለያዩ ለውጦችን ያደረገበት ዓመት ነበር።

አቶ ጉማቸው እንዳብራሩት ባንኩን ከነበረበት ፈተና በማውጣት አሁን ወዳለበት ደረጃ ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት የተደረገ ሲሆን፡ የባንኩን አቋም ለማስተካከል በበጀት ዓመቱ በርካታ ውሳኔዎች መወሰናቸውን ገልጸዋል። ከተላለፉት ውሳኔዎች ውስጥ በሶስተኛው ሩብ ዓመት አዲስ ፕሬዚዳንት መሾሙ ዋነኛው እንደነበር ተገልጿል። የተበላሹ ብድሮች ክምችትን ለመቀነስም የተሰራው ሥራ እንዲሁም ትርፋማነትን ማሻሻል ባንኩ በበጀት ዓመቱ ካከናወናቸው ተግባራት መካከል በዋናነት የሚጠቀሱ መሆኑን በሪፓርቱ ላይ ተመልክቷል።

የባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚገልፀው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ካለፈው በጀት ዓመት የብር 4.3 ቢሊዮን ወይም የ19.9 በመቶ ጭማሪ በማስመዝገብ ብር 26.0 ቢሊዮን መድረስ ችሏል። በተመሳሳይ የተቀማጭ ሂሳብ ደንበኞች ቁጥር የ 39.7 በመቶ እድገት በማስመዝገብ 1.6 ሚሊዮን ደርሷል። የብድር ክምችትም ብር 22.2 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በብር 4.4 ቢሊዮን ወይም በ24.4 በመቶ እድገት አስመዝግቧል። በተጨማሪም የባንኩ አጠቃላይ ሃብት ብር 33.1 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በ 22.8 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። የባንኩ አጠቃላይ ካፒታል 19.1 በመቶ እድገት በማስመዝገብ ብር 4.5 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን የባንኩ የተከፈለ ካፒታል በ8.7 በመቶ በማደግ ብር 3.2 ቢሊዮን ደርሷል።

ብርሃን ባንክ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ከታክስ በፊት ብር 583.4 ሚሊዮን ማትረፍ የቻለ ሲሆን ይህም ካለፈው የበጀት ዓመት ትርፍ ጋር ሲነጻጸር የ72.8 በመቶ እድገት አስመዝግቧል።

የባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት ላይ እንደተገለፀው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባንኩ አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ ሊያደርግ ይችላል ብሎ ያመነበትን 3ኛውን ስልታዊ እቅድ ያዘጋጀ ሲሆን፥ ከዚሁም ጋር ተያይዞ የድርጅታዊ መዋቅር ክለሳ በማድረግ እ.ኤ.አ. ከ2022/23 በጀት ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ያደርጋል። በሌላ በኩል ባንኩ በአዲስ አበባ ከተማ የፋይናንስ ተቋማት ማዕከል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለዋና መስሪያ ቤት ህንፃ ግንባታ ለተቀበለው ቦታ የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ ተረክቧል። የቦርድ ሰብሳቢው እንደገለፁት ከሆነ በቅርቡ ደማቅ በሆነ ስነስርዐት በቦታው ላይ ለህንፃ ግንባታው የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል። በተመሳሳይ ባንኩ በወላይታ ሶዶ ከተማ ያገኘውን ቦታ ርክክብ ያካሄደ ሲሆን የግንባታውንም መሰረት ድንጋይ አስቀምጧል።

በመጨረሻም የድይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢው ላባንኩ ባለአክሲዮኖች ፥ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፥ ለደንበኞች፥ ለባንኩ አመራርና ሠራተኞች በሙሉ ባንኩ ላስመዘገበው ስኬት ላደረጉት አስተዋፅኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።