ብርሃን ባንክ የ 41.2 በመቶ የትርፍ እድገት አስመዘገበ ; የተከፈለ ካፒታሉን በእጥፍ ለማሳደግ ወስኗል

  • ብርሃን ባንክ የ 41.2 በመቶ የትርፍ እድገት አስመዘገበ
  • የተከፈለ ካፒታሉን በእጥፍ ለማሳደግ ወስኗል

ብርሃን ባንክ 10ኛ መደበኛ እና 5ኛ ድንገተኛ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ታህሳስ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ አካሂዷል። በጉባኤው ላይ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ጉማቸው ኩሴ እ.ኤ.አ. ሰኔ 30 ቀን 2019 የተጠናቀቀውን  የባንኩን ዓመታዊ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ለባለአክሲዮኖች አቅርበዋል። በቀረበው ሪፖርት መሰረት በበጀት ዓመቱ በሃገራችን የታየው የፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተግዳሮቶች ከፍተኛ የነበሩ ቢሆንም ባንኩ የተገኙ እድሎችን በአግባቡ ለመጠቀም እና ተግዳሮቶችን ለመሻገር የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ቀይሶ ተግባራዊ በማድረጉ በሁሉም የስራ ዘርፎች አጥጋቢ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉ ተገልጿል።

በቀረበው ሪፖርት መሰረት ባንኩ ከግብር በፊት ብር 580.1 ሚሊዮን ትርፍ ማስመዝገበ የቻለ ሲሆን ይህም አፈጻጸም ካለፈው የበጀት ዓመት ጋር በንጽጽር ሲታይ የ ብር 169.1 ሚሊዮን ወይንም የ 41.2 በመቶ እድገት አሳይቷል። በመሆኑም የባንኩ ብር 1000 ዋጋ ያለው አክሲዮን የትርፍ መጠኑ ብር 246.5 የደረሰ ሲሆን ይህም ባንኩ ባለፈው የበጀት ዓመት ካስመዘገበው አፈጻጸም ጋር ሲወዳደር የተሻል ሆኗል።

ሃብትን በማሰባሰብ ረገድ በበጀት ዓመቱ የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ ብር 14.9 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ካለፈው የበጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ ብር 4.1 ቢሊዮን ወይንም የ37.8 በመቶ እድገት ማስመዝገብ ችሏል። በተመሳሳይም በበጀት ዓመቱ ባንኩ 161.7 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሪ መሰብሰብ የቻል ሲሆን ይህ ውጤት በአለፈው በጀት ዓመት ከተመዘገበው ጋር ሲነጻጸር የ 53.2 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወይም የ 49 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡  በተጨማሪም የባንኩ የብድር ክምችት ባለፈው በጀት ዓመት ከነበረው ከብር 7.2 ቢሊዮን በብር 3.02 ቢሊዮን ወይንም በ42.1 በመቶ በማደግ ብር 10.2 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን የባንኩ አጠቃላይ ሃብት ደግሞ ከአለፈው ዓመት በ36.3 በመቶ እድገት በማስመዝገብ ብር 19.2 ቢሊዮን ደርሷል፡፡  በተጨማሪም የባንኩ አጠቃላይ ካፒታል ከአለፈው ዓመት በ27 በመቶ በማደግ ብር 2.8 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን  የተከፈለ ካፒታል ደግሞ የ 17 በመቶ እድገት በማሳየት ብር 2 ቢሊዮን ደርሷል፡፡ ይህም ብርሃን ባንክ በበጀት ዓመቱ በሁሉም የአፈጻጸም ዘርፎች አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን በተጨባጭ ያሳያል።

ባንኩ በበጀት ዓመቱ ውስጥ 18 አዳዲስ ቅርንጫፎችን የከፈተ ሲሆን አጠቃላይ የቅርንጫፍ ስርጭቱን 200 ማድረስ ችሏል።  የባንኩ የደምበኞች ቁጥር ደግሞ በ 133 ሺህ ወይም በ 25.5 በመቶ በማደግ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ 657,026 ደርሷል። በተጨማሪም ባንኩ የሞባይል ቶፕ አፕ እና አፕሊኬሽን ቤዝድ ሞባይል ባንኪንግ አገልግሎቶች እንዲሁም የማስተር ካርድ የክፍያ አገልግሎት በመጀመር ደንበኞች የተቀላጠፈ እና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡

በተጨማሪም በእለቱ 5ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ያደረገው ባንኩ የባንኩን የተከፈለ ካፒታል በዕጥፍ በማሳደግ ወደ 4 ቢሊዮን ለማድረስ ወስኗል፡፡

በመጨረሻም ባንኩ በቀጣይ ዓመታት አሁን ያስመዘገበውን ውጤት ለማስቀጠል የተለያዩ ስልቶችን ነድፎ እንደሚንቀሳቀስ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አስታውቀዋል።Demos

Layout

Wide
Boxed
Scroll up