የብርሃን ባንክ 411 ሚሊዮን ብር አተረፈ (ምንጭ፡ ሪፖርተር- ህዳር  3/2011 ዓ.ም)

የብርሃን ባንክ 411 ሚሊዮን ብር አተረፈ

ከሁለት ዓመት በፊት (በ2008 ሒሳብ ዓመት) የትርፍ መጠኑን በ152 በመቶ ማሳደግ ችሎ የነበረው ብርሃን ባንክ፣ በ2010 የሒሳብ ዓመት 411 ሚሊዮን ብር አተረፈ፡፡

ባንኩ ኅዳር 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንደተገለጸው፣ ባንኩ በ2010 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ያገኘው የትርፍ መጠን 411 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህ የትርፍ መጠን ከ2009 የሒሳብ ዓመት አንፃር ሲታይ የ37 ሚሊዮን ብር ወይንም የአራት በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡

ባንኩ በ2008 ሒሳብ ዓመት 349.8 ሚሊዮን ብር ባስመዘገበበት ወቅት የትርፍ ዕድገቱ ከቀዳሚው የሒሳብ ዓመት አንፃር ከ150 በመቶ በላይ ጨምሮ ስለነበር ከፍተኛ የተባለ የትርፍ ዕድገት ሆኖ መጠቀሱ አይዘነጋም፡፡

በ2009 ሒሳብ ዓመት ያገኘው ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት አንፃር የ34 በመቶ ብልጫ ነበረው፡፡ የ2010 ሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙ ግን እንደቀድሞው ሳይሆን ቅናሽ አስመዝግቧል፡፡

በባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት ላይ እንደተጠቀሰው፣ በባንኩ የተመዘገበው የአራት በመቶ የትርፍ ቅናሽ ከአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በተከሰተ ተግዳሮት ስለመሆኑም ተጠቅሷል፡፡ ‹‹ይኼ ውጤት የተመዘገበው በአገራችን የማኅበራዊና የፖለቲካ ሁኔታ ከምን ጊዜውም በተለየ ባልተረጋጋበትና የባንክ ኢንዱስትሪው ላይ ሌሎች በርካታ ተግዳሮቶች የተጋረጡበት ወቅት መሆኑ እሙን ነው፤›› በማለት በሪፖርቱ ላይ አስቀምጧል፡፡

ባንኩ የትርፍ መጠኑ ቢቀንስም በሌሎቹ የባንክ ሥራዎች አፈጻጸሙ ውጤታም ስለመሆኑ የባንኩ የሒሳብ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

ስኬታማ አፈጻጸም ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥ የተቀማጭ ገንዘቡን መጠን በ3.2 ቢሊዮን ብር (በ41.6 በመቶ) በማሳደግ 10.9 ቢሊዮን ብር ማድረሱ አንዱ ነው፡፡ የተቀማጭ ገንዘብ ደንበኞቹ በ42.6 በመቶ በመጨመር 523,705 ማድረስም ችሏል፡፡

ባንኩ ለደንበኞቹ የሰጠው ብድር 7.2 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይኼም ከቀዳሚው ዓመት በ33 በመቶ ብልጫ እንዳለው ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ የሀብት መጠኑም በ33.5 በመቶ ከፍ ብሎ 14 ቢሊዮን ብር መድረሱ በስኬትነት ተጠቅሷል፡፡

 

 Demos

Layout

Wide
Boxed
Scroll up