ብርሃን ባንክ የብድር ወለድ ምጣኔ ቅናሽ አደረገ

ጋዜጣዊ መግለጫ

የብርሃን ባንክ አ.ማ. የኮቪድ-19 ተጽእኖን ለማቃለል በማሰብ ከ 0.5% እስከ 4% የሚደርስ የብድር ወለድ ምጣኔ ቅናሽ እ.ኤ.አ ከሜይ 18, 2020 ጀምሮ ተግባራዊ ማድረጉን አስታወቀ። የወለድ ቅናሽ ማስተከካያውም በተለያዩ ኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ኮቪድ-19 ያስከተለውን ተጽእኖ ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ሲሆን ሁሉም የብድር ዘርፎች ማለትም የግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ የአገር ውስጥ፣ ንግድና አገልግሎት፣ የወጪ ንግድ፣  ሕንፃና ግንባታ፣  የግል ብድር ዘርፎች የወለድ ምጣኔ ቅናሽ ተጠቃሚ ሆነዋል።

የወለድ ምጣኔ ቅናሹ በተለይም በኮቪድ-19 ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ዘርፎች ከፍተኛውን የወለድ ምጣኔ ቅናሽ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ለአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ላኪ ዘርፍ የ4% የወለድ ምጣኔ ቅናሽ የተደረገ ሲሆን እንዲሁም ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፎች ደግሞ የ3.5% ቅናሽ ተደርጓል። በተጨማሪም ለእነዚህ የኢኮኖሚ ዘርፎች የስድስት ወራት የፍሬ ብድር እና የወለድ ክፍያ የእፎይታ ጊዜ ከሜይ 18 2020 ጀምሮ እንዲደረግላቸው ባንኩ ወስኗል፡፡ በሌላም በኩል ተበዳሪዎቻችን በኮቪድ-19 ጫና ምክንያት የብድር ክፍያ ማራዘሚያ ጥያቄ ቢያቀርቡ ጥያቄያቸው እንደሁኔታው እየታየ የሚስተናገድ ይሆናል።

ባንኩ ይህንን የወለድ ምጣኔ ቅናሽ በማድረጉ በዓመት ሊያገኝ የሚችለውን ወደ ብር 100 ሚሊዮን የሚሆን የወለድ ገቢ የሚያሳጣው መሆኑ ታውቋል። ይህም ውሳኔ ከባንኩ  እድሜ እና አቅም አንፃር ሲታይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ ብሔራዊ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ባንኩ የበኩሉን አስተዋፅኦ ከማበርከት አንፃር የሚሄድበትን ርቀት እና ቁርጠኝነት  ያመለክታል፡፡

የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) በአገራችን ከተከሰተ ጀምሮ ባንካችን ማሕበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን ሰፊውን ማህበረሰብ እና የባንኩን ደንበኞች ማዕከል ያደረጉ በርካታ ተግባራትና ድጋፎች ከዚህ ቀደም ማከናወኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህም አንፃር ቀደም ሲል  የ Letter of Credit ማራዚሚያ ኮሚሽን ሙሉ በሙሉ ማንሣቱን፣ የብድር ማራዘሚያ ኮሚሽንና የተጨማሪ ወለድ ማንሣቱ፤ በአዲስ አበባ እና ክልል ከተሞች በ35 ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች የንፅህና አገልግሎት መስጫ የውሃ ታንከሮችን ማዘጋጀቱ እና እንዲሁም ለጤና ሚኒስቴር ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ብር 3 ሚሊዮን ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በመጨረሻም ባንካችን ለወደፊቱም የወረርሽኙን ተጽዕኖ ለመቅረፍ ተመሣሣይ ድጋፎችን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በትህትና እንገልፃለን፡፡

 

እንደስማችን ብርሃን ነው ስራችን!

ግንቦት 13, 2012 ዓ/ምDemos

Layout

Wide
Boxed
Scroll up