ብርሃን ባንክ አ.ማ. የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19)ን ለመከላከል የተለያዩ እርምጃዎችን ወሰደ፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫ

መጋቢት 17/2012 ዓ.ም

ጋዜጣዊ መግለጫ

ብርሃን ባንክ አ.ማ. የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19)ን ለመከላከል የተለያዩ እርምጃዎችን ወሰደ፡፡

 

እንደሚታወቀው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአለማችን በከፍተኛ ፍጥነት በመዛመት በርካታ ህይወት የቀጠፈው የኮሮና ቫይረስ -በሳይንሳዊ ስያሜው ኮቪድ 19 በርካታ ሃገራት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል፡፡ የበሽታውን በስፋት የመዛመት እና እያስከተለ ያለውን ሰብዓዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት በአለም ስጋትነት ተፈርጇል፡፡  በዚህም የአለም ጤና ድርጅትን ጨምሮ በርካታ ታላላቅ ተቋማት በሽታውን ለመከላከል ይረዳሉ ያሏቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች በመጠቆም ላይ ቢሆኑም ቫይረሱ ስርጭቱን እየጨመረ በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋቱን ቀጥሏል፡፡ በሃገራችንም በበሽታው  የተጠቁ ዜጎች እና የውጭ ሃገራት ግለሰቦች መገኘታቸው ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ መንግስት በተለያዩ ሚድያዎች የጥንቃቄ መንገዶችን ከማስተላለፍ ባለፈ ቅድመ ጥንቃቄን ማዕከል ያደረጉ በርካታ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ላይ ይገኛል፡፡

ብርሃን ባንክ የበሽታውን አስከፊነት በመገንዘብ እና  ከዚህ በኋላ ቫይረሱ በዜጎች ላይ ይበልጥ ቢስፋፋ የሚያስከትለውን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት እንዲሁም የጉዳዩን አንገብጋቢነት በመገንዘብ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ውሳኔዎች አሳልፏል፡፡

ለክቡራን ደንበኞቹ፡-

  1. በአሁኑ ወቅት ከኮሮና ቫይረስ መስፋፋት ጋር በተያያዘ በዓለም ዓቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ የተፈጠረውን ተግዳሮት ከግምት ውስጥ በማስገባት   በ ኤል ሲ ማራዘሚያ ኮሚሽን ላይ ባንኩ ሲያስከፍል የነበረውን ክፍያዎች እ ኤ አ ከማርች 26, 2020 ጀምሮ ለ60 ቀናት ሙሉ በሙሉ አንስቷል፡፡
  2. የባንኩ ተበዳሪዎች በኢኮኖሚው መቀዛቀዝ ሳቢያ ሊያጋጥማቸው የሚችለውን የብድር መክፈል አቅም ውሱንነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ለብድር መክፈያ ጊዜ ማራዘሚያ (ሪስኬጁሊግ) ቀደም ሲል ባንኩ ሲያስከፍል የነበረውን ተጨማሪ የወለድ እና የአገልግሎት ክፍያዎች ከተጠቀሰው ቀን ጀምሮ ለሚቀጥሉት 60 ቀናት ባንኩ ሙሉ በሙሉ አንስቷል፡፡
  3. የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ከሰዎች ጋር የሚኖር የማህበራዊ ርቀትን ከግምት ውስጥ በማስገባት በባንካችን ቅርንጫፎች የተስተናጋጅ ደንበኞችን ቁጥር ከመቀነስ አንፃር ከመጋቢት 17 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በባንኩ ኤ.ቲ.ኤም የሚጠቀሙ የባንኩ ደንበኞች ገንዘብ ሲያወጡ ባንኩ ያስከፍል የነበረው የአገልግሎት ክፍያ ሙሉ በሙሉ ተነስቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የባንኩ ደንበኞች በቀን እስከ ብር10,000 (አስር ሺህ ብር) ወጪ ማድረግ የሚችሉ በመሆኑ ደንበኞች ወደ ቅርንጫፍ መምጣት ሳያስፈልጋቸው በኤቲኤም ይጠቀሙ ዘንድ እናበረታታለን፡፡ በተጨማሪም ለተጠቃሚ ደንበኞች ደህንነት ሲባል የባንኩ ኤ.ቲ.ኤም ማሽኖች በየጊዜው በአልኮል እንዲፀዱ ይደረጋል፡፡
  4. ከ መጋቢት 17 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በባንኩ ዋና መስሪያ ቤትና በሁሉም የባንኩ ቅርንጫፎች የእጅ መታጠቢያ ውሃ ከሳሙና ጋር የሚቀርብ ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱ ለደንበኞች ለእጅ ንፅህና መጠበቂያነት የሚያገለግሉ አልኮል እና ሳኒታይዘር እንደ አቅርቦቱ ሁኔታ ይጠቀሙ ዘንድ በቅርንጫፎች ውስጥ እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡

ለማህበረሰቡ፡-

  1. መላው ማኅበረሰባችን የእጅ ንፅህናውን በመጠበቅ ከበሽታው መከላከል ይችል ዘንድ ውሃ የመያዝ አቅማቸው 2000 ሊትር የሆኑ የውሃ ታንከሮች ህዝብ በሚበዛባቸው እና ለማኅበረሰቡ አመቺ በሆኑ አስር (10) የተመረጡ የአዲስ አበባ ዋና ዋና ስፍራዎች (በጦር ሃይሎች፣ በአውቶቢስ ተራ፣ ፒያሳ ጊዮርጊስ አካባቢ፣ ጀሞ አደባባይ፣ አያት አደባባይ፣ አየር ጤና፣ አራት ኪሎ፣ ቦሌ፣ አቃቂ እና ቃሊቲ አካባቢ) ከሐሙስ መጋቢት 17 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ተተክለው አገልግሎት መስጠት የሚጀምሩ ይሆናል፡፡
  2. መንግስት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያደርገውን አገራዊ እንቅስቃሴ ለመደገፍ የመላው ኅብረተሰብ ርብርብ የሚያስፈልግ በመሆኑ ብርሃን ባንክም ከዚህ ቀደም እንደሚያደርገው ሁሉ የማኅበራዊ ሃላፊነቱን ከመወጣት አኳያ ብር 3 ሚሊዮን (ብር 3,000,000) ለጤና ሚንስቴር ድጋፍ ለማድረግ ወስኗል። የተደረገውም ድጋፍ በመንግስት በኩል አቅም ለሌላቸውና ራሳቸውን ማገዝ ለማይችሉ የማኅበረሰቡ ክፍሎች ተደራሽ እንደሚሆን ይጠበቃል።
  3. ከጤና ሚንስቴር ጋር በመመካከር የደንበኞችን የሙቀት መላኪያ መሳሪያ (በሕክምና አጠራሩ Infrared non-contact thermo-meter for corona screening) በዋናው መስሪያ ቤትና በቅርንጫፎች በማስቀመጥ የሙቀት መጠናቸው ከተቀመጠው መስፈርት (standard) በላይ የሆኑትን የመለየቱን ሥራ ለማከናወን እቅድ ተይዟል። 

ለባንኩ ሰራተኞች፡-

  1. ነፍሰጡሮች   እንዲሁም እድሜያቸው ከ55 ዓመት በላይ የሆኑ የባንኩ ሰራተኞች የኣመት እረፍታቸውን በማይነካ ሁኔታ እና ሙሉ ጥቅማ ጥቅማቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከመጋቢት 17 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለ15 (አስራ አምስት ) ቀናት በቤታቸው እንዲቆዩ ተወስኗል፡፡ ይህም ሆኖ ከዚህ በኋላ እንደሚኖረው አጠቃላይ ሃገራዊ ሁኔታ እየታየ እረፍቱ ለወደፊቱ ሊታደስ የሚችል ይሆናል፡፡ ሆኖም እንደ ሁኔታው እየታየ እቤታቸው የሚቆዩ ሰራተኞቻችን ከቤት ሆነው የሚሰሩበት ሁኔታ ይመቻቻል።
  2. ለሁሉም የባንኩ ሰራተኞች እንደ ሥራው ባህሪይ የአፍ መሽፈኛ (ማስክ) እና የእጅ ጓንት የማዳረሱ ስራ እየተሰራ ይገኛል።
  3. ባንኩ የማህበራዊ ርቀትን ከመጠበቅ እና የቫይረሱን ስርጭት ከመገደብ እና ከመከላከል አንፃር በመደበኛነት ሰራተኞቹን በማሰባሰብ የሚያከናውናቸውን አጫጭር እና ረዣዝም ስልጠናዎች እንዲሁም በርካታ ተሳታፊዎች የሚገኙባቸውን የአመራር ስብሰባዎች ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጡ ወስኗል፡፡

በመጨረሻም መላው የባንኩ ሰራተኞች፣ ደንበኞችና ማኅበረሰባችን ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚስያስፈልጉ ተገቢ ጥንቃቄዎችን በማድረግ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው አገራዊ እንቅስቃሴ የበኩላችንን ኃላፊነት እንድንወጣ በአክብሮት እንጠይቃለን።

 

ብርሃን ባንክ አ.ማ

እንደ ስማችን ብርሃን ነው ሥራችን!Demos

Layout

Wide
Boxed
Scroll up