ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ በ2016 /17 በጀት ዓመት ብር 471.4 ሚሊዮን አተረፈ

የብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ ባለአክሲዮኖች ስምንተኛ መደበኛና አራተኛ ድንገተኛ ጉባኤ ቅዳሜ ኅዳር 30 ቀን 2010 ዓም በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል። የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ሰለሞን አለምሰገድ ይፋ ባደረጉት ሪፖርት  እኤአ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ባንኩ በሁሉም የስራ ዘርፎች የላቀ የስራ አፈጻጸም በማስመዝገብ ጠንካራና ተፎካካሪ ባንክ መሆኑን አስመስክሯል ሲሉ ገልጸዋል።

አያይዘውም በተገባደደው የበጀት ዓመት ባንኩ ከግብር በፊት ብር 471.4 ሚሊዮን ትርፍ ማስመዘገብ መቻሉንና ይህም ከአለፈው የበጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር  የብር 121.6 ሚሊዮን ወይም 34.8 በመቶ የሆነ ከፍተኛ ብልጫ ያለው መሆኑን አስታውቀዋል። በዚሁ በጀት ዓመት ባንኩ ተጨማሪ አክሲዮኖቸን በመሸጥ የተከፈለ ካፒታሉን  ወደ ብር 1.4 ቢሊዮን ያሳደገ ሲሆን ከአለፈው የበጀት ዓመት የ91.1 በመቶ የሆነ ከፍተኛ ጭማሪ  ማሳየቱን ገልጸዋል። ምንም እንኳን ባንኩ የተከፈለ ካፒታሉን በከፍተኛ መጠን ቢያሳድግም የባንኩ ባለአክሲዮኖች ባዋጡት መዋዕለ ነዋይ መጠን የሚያገኙት የትርፍ ድርሻ RoE በበጀት ዓመቱ 32.8 ሆኗል ፤ ይህም አመርቂ ውጤት መሆኑን አስታውቀዋል።በተመሳሳይ መልኩም ባንኩ የባለአሲዮኖቹን ቁጥር በ53.6 በመቶ በማሳደግ በበጀት ዓመቱ 14,841 አድርሷል።

የብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ  ፕሬዘዳንት የሆኑት አቶ አብርሃም አላሮ በበኩላቸው የተጠናቀቀው የበጀት ዓመት  ከፍተኛ የገበያ ውድድርና በባንኩ ክፍለ ኢኮኖሚ በርካታ ተግዳሮቶች የነበሩበት ዓመት መሆኑን ጠቅሰው በበጀት ዓመቱ  ባንኩ  በሁሉም የስራ ዘርፍ  ያስመዘገበው የስራ አፈጻጸም ውጤት እጅግ አመርቂ መሆኑን ገልጸዋል። ባንኩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ጠቅላላ ተቀማጭ ሂሳቡን ወደ ብር 7.6 ቢሊዮን ማሳደጉንና ይህም ከአለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር የ 43.3 በመቶ የሆነ ከፍተኛ ዕድገት ማሳየቱን አስታወቀው በተመሳሳይ መልኩም ባንኩ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው የብድር ክምችት በበጀት ዓመቱ ብር 5.4 ቢሊዮን መድረሱን ይህም ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የ42.1 በመቶ  የሆነ ከፍተኛ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።

በአገሪቱ እየታየ ያለው የውጭ ምንዛሬ እጥረት በበጀት ዓመቱም የቀጠለ በመሆኑ ባንኩ 124.9 ሚሊዮን አሜሪካን ዶላር የሰበሰበ ሲሆን ይህም ከአለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ 4.5 በመቶ የሆነ መጠነኛ ቀናሽ ማሳየቱን አስታውቀዋል።

አቶ አብርሃም አያይዘውም ባንኩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 56 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት በመላ አገሪቱ ያሉትን የቅርንጫፎች ቁጥር ወደ 161 ማድረሱን ገልጸው ይህም ከአለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 53.3 በመቶ የሆነ ከፍተኛ ብልጫ እንዳለው አስረድተዋል። በተጨማሪም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት  የባንኩ ደንበኞች ቁጥር ከአለፈው ዓመት ከነበረው የ88 በመቶ የሆነ ከፍተኛ ዕድገት በማስመዝገብ 367,379 መድረሱን ገልጸዋል።

ባንኩ እያስመዘገበ የመጣውን ከፍተኛ የሆነ ሁለንተናዊ ዕድገት ተከትሎ 1,154 ተጨማሪ ሰራተኞችን በበጀት ዓመቱ የቀጠረ ሲሆን ይህም ባንኩ ያለውን አጠቃላይ የሰው ሃብት ቁጥር ወደ 2,865  ማሳደጉን ፕሬዘዳንቱ  ጠቁመው  ከአለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ 36.6 በመቶ የሆነ ከፍተኛ  ዕድገት ማስመዝገቡን ገልጸዋል። አያይዘውም ባንኩ ለሰው ሃብቱ ከሚሰጠው ልዩ ትኩረት የተነሳ በበጀት ዓመቱ ዲሎይ’ት የተባለው ታዋቂ ዓለምአቀፍ አማካሪ ድርጅት ባካሄደው ጥናት ባንኩ ሠራተኞች ሊሰሩበት የሚመርጡት ተቋም በመባል መመረጡን ገልጸዋል። አቶ አብርሃም በቀጣዩ የበጀት ዓመት ባንኩ እሰካሁን የመጣበትን የስኬት ጉዞ ሊያስቀጠል የሚችል ስተራተጂ ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ባንኩ የበለጠ ውጤት እንደሚያመጣ ጽኑ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

 Leave a Reply

Demos

Layout

Wide
Boxed
Scroll up