- July 1, 2017
- Posted by:
- Category: News

ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ በዘመናዊው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሥርአት ውስጥ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት የሚያስችለውን የክፍያ አገልግሎት ሥርአት ስምምነት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር ሰኔ 14 ቀን 2009 ዓ.ም በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና መሥሪያ ቤት ተፈራርሟል፡፡ ስምምነቱን የፈረሙት የብርሃን ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም አላሮ እና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኤርምያስ እሸቱ ናቸው፡፡
በፊርማ ሥነ ሥርአቱ ላይ የብርሃን ባንክ ፕሬዝዳንት ባደረጉት ንግግር ፣ በአሁኑ ወቅት 352,000 የሚሆኑ የባንኩ ደንበኞች ብር 7.4 ቢሊየን ማስቀመጣቸውንና በተለያዩ ዘርፍ የተሰማሩ ከ4,496 በላይ የሚሆኑ ደንበኞች ደግሞ ብር 5.1 ቢሊየን የብድር አገልግሎት ማግኘታቸውን አስታውሰዋል፡፡ አያይዘውም ባንኩ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት በመስጠቱና የደንበኞችን አመኔታን በማግኘቱ አሁን ደግሞ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር ያደረገው የክፍያ አገልግሎት ስምምነት የበለጠ አገልግሎቱን በጥራትና በብዛት ለመስጠት ዕድል እንደሚሰጠው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኤርምያስ እሸቱ በፊርማው ሥነ ሥርአት ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባህላዊዉን የግብይት ሥርአት በማስቀረት በአዲስ አስተሳሰብ ከአምራቹ አርሶ አደር እስከ ላኪና ተቀባዩ ድረስ ሁሉም የገበያው ተዋንያን በዘመናዊ የግብይት ሥርአት እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻሉን አስምረውበት ፤ ከስምምነቱ በኋላ በዚህ የግብይት ሂደት ውስጥ የብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ ድርሻ በመውሰድ የበኩሉን ሚና ሲጫወት የክፍያ ሥርአቱን ይበልጥ ለማቀላጥፍና ለማዘመን የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት አስተዋጽዖ እንደሚኖረው አስገንዝበዋል፡፡
በመጨረሻም ስምምነቱን የፈረሙት ሁለቱም ወገኖች ለወደፊት የሚኖራቸው የሥራ ግንኙነት የበለጠ እንደሚጠናከርና ለውጤት እንደሚበቃ አረጋግጠዋል፡፡