ብርሃን ባንክ የ150 በመቶ ትርፍ እድገት አስመዘገበ

ብርሃን ባንክ 15ተኛ መደበኛ እና 6ተኛ አስቸኳይ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ሐሙስ ጥቅምት 7 ቀን 2017 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ አካሄደ፡፡ በጉባኤው ላይ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ኤሊጎ ለገሰ እ.ኤ.አ. ሰኔ 30 ቀን 2024 የተጠናቀቀውን የባንኩን ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለባለአክሲዮኖች አቅርበዋል፡፡

አቶ ኤሊጎ በሪፖርታቸው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የባንኩ የሥራ ክንውን በተለይ ከትፋማነት አንጻር በኢንዱስትሪው ካሉ ባንኮች አኳያ ሲታይ ያነሰ የነበረ እና  የባለአክሲዮኖች የተጣራ የትርፍ ተከፋይም እጅግ አነስተኛ እንደነበር ገልጸዋል። አቶ ኤሊጎ በመቀጠል የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ባንኩን በኢንዱስትሪው ተወዳዳሪና ትርፋማ ለማድረግ፣ በሥራ አፈጻጸማቸው፣ በትምህርት ዝግጅታቸው እንዲሁም በሥነ-ምግባራቸው የተመሰገኑ የባንክ ባለሙያ በማፈላለግ  ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድርጎ ታኀሣሥ 29 ቀን 2016 ዓ.ም.  መሾሙን፣  ዋና ሥራ አስፈጻሚው ሥራ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በተከናወኑ ልዩ ልዩ ተግባራት፣ በተዘረጉ የአሠራር ሥርዓቶች እና በተከናወኑ ከፍተኛ የክትትል ተግባራት፣ የተበላሹ ብድሮች በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ እንዲሁም ውጤታማ የወጪ ቁጥጥር ስትራቴጂ በመተግበር  የባንኩን ትርፋማነት ለማሳደግ መቻሉን አሳውቀዋል።

 አቶ ኤሊጎ  ባንኩ በጀት ዓመቱን ሲዘጋ ከግብር በፊት ብር 1.51 ቢሊዮን ትርፍ ማስመዝገብ የቻለ መሆኑን ገልጸው፣ ይኽም ካለፈው የበጀት ዓመት ትርፍ ጋር ሲነጻጸር 150 በመቶ የተጠጋ እድገት ያለው መሆኑን እንዲሁም ከ2023/24 የበጀት ዓመት አጋማሽ ጋር ሲነጻጸር ደግሞ የ395 በመቶ ብልጫ እድገት ማሳየቱን ጠቁመዋል።  በመሆኑም ባንኩ ለባለአክሲዮኖቹ የሚከፍለው አጠቃላይ የትርፍ ተከፋይ (Basic RoE) መጠን በአንድ አክሲዮን 35.03 በመቶ በማድረስ ከፍተኛ ውጤት ሊያስመዘግብ መቻሉን ገልጸዋል።

ለተጨማሪ መረጃ በ 011 6 507707 እና 0116 185712 ይደውሉ