ብርሃንባንክ የዋና መስሪያ ቤት ህንጻ አርኪቴክቸራል ዲዛይን አሸናፊዎች የሽልማት መርሃግብር አካሄደ

ብርሃን ባንክ በአዲስ አበባ የባንኮች ዋና መስሪያ ቤት ህንፃዎች በሚገኙበት በሰንጋተራ አካባቢ የሚገነባው የዋና መስሪያ ቤት ሕንጻ የአርኪቴክቸራል ዲዛይን ውድድር በማካሄድ አሸናፊ ለሆኑት የሽልማት መርሃግብር አካሂዷል፡፡

መርሃግብሩ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ምክትል ገዢ አቶ ሰለሞን ደስታ፣ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ጉማቸው ኩሴ፣ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ግሩም ፀጋዬ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ ባለ አክሲዮኖች፣ የባንኩ ከፍተኛ የስራ አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በስካይ ላይት ሆቴል ተካሂዷል፡፡

የብርሃን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ግሩም ፀጋዬ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት፤ እ.አ.አ. በ2009 ዓ.ም የተመሠረተው ብርሃን ባንክ በአሁኑ ጊዜ ወደ 2 ሚሊዮን ገደማ ደንበኞች ያሉትና የቅርንጫፎቹን ቁጥር ከ350 በላይ ያደረሰ የ13 ዓመት ወጣት ባንክ መሆኑን ገለጸዋል፡፡ በተጨማሪም ባንኩ ለደንበኞቹ የሚሰጠውን አገልግሎት ይበልጥ ለማዘመንና ስራውን በቀልጣፋ ሁኔታ ለማከናወን የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ዘርግቶ እየሰራ እንደሆነና የዋና መስሪያ ቤት ህንፃ ግንባታውም በስትራቴጂክ ዕቅዱ ውስጥ አንዱና ዋነኛው አንኳር ተግባራት እንደሆነ ገለጸዋል፡፡

አቶ ግሩም አክለውም ባንኩ በአዲስ አበባ የፋይናንስ ተቋማት መገኛ በሆነው ሰንጋተራ አካባቢ 5400 ካ.ሜ ስፋት ያለው መሬት ተረክቦ የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ የዋና መስሪያ ቤት ህንጻ ግንባታውን ለማከናውን በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የዚሁ ህንፃ ግንባታ የመጀመሪያው አካል የሆነውን የህንፃውን ዲዛይን የመምረጥ ሂደት በተሳካ ሁኔታ ያካሄደ ሲሆን ቀጣይ ሂደቶች ሲጠናቀቁ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ሕንፃዎች  በቴክኖሎጂ የበለፀገ ዘመናዊ ሰማይጠቀስ ሕንፃ በመገንባት ለአዲስ አበባ ከተማ ተጨማሪ ብርሃን እና ውበት በመጨመር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል፡፡

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ጉማቸው ኩሴ በበኩላቸው የባንኩ ሃብት ብር 43.7 ቢሊየን እና የተከፈለ ካፒታል 3.3 ቢልየን መድረሱን ገልፀዋል፡፡  በተጨማሪም ባንኩ በያዘው የበጀት ዓመት ተግባራዊ ባደረገው የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ መሰረት የተቀማጭ ገንዘብ መጠንን ከብር 100 ቢሊየን እንዲሁም የብድር ክምችቱን ከብር 90 ቢሊየን በላይ ለማድረስ የታቀደ ሲሆን፤ የተከፈለ ካፒታሉን ወደ 7 ቢሊየን ለማድረስ መታቀዱን ገልፀው፤  የባንኩን ሃብትም ከብር 120 ቢሊየን በላይ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡  በቀጣይም ባንኩ በኢንደስትሪው ውስጥ ብቁ  ተወዳዳሪ ሆኖ መቀጠል እንዲችል በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ያለውን የቅርንጫፍ ተደራሽነት ለመጨመር እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገለጸዋል፡፡ 

በመጨረሻም ባንኩ የተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎችን በማለፍ አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ የባንኩን ባለአክሲዮኖች፤ አመራሮች እና ደንበኞች ላደረጉት አስተዋጽዖ ምስጋናን አቅርበዋል፡፡

አቶ ሰለሞን ደስታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ የዕለቱ የክብር እንግዳ የነበሩ ሲሆን በዲዛይን ውድድሩ አንደኛ ለወጣው የሰርተፊኬትና የዋንጫ ሽልማት አበርክተዋል፡፡

በዝግጅቱ ላይ ለባንኩ የዋና መስሪያ ቤት ህንጻ የአርኪቴክቸራል ዲዛይን ውድድር የቀረቡት ዲዛይኖች ልደታ አካባቢ በሚገኘው ህንፃ ኮሌጅ ጊቢ ውስጥ ከግንቦት 05 አስከ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ለህዝብ ዕይታ እንደሚቀርቡም ተገልጿል፡፡

የዕለቱ ተጋባዥ እንግዳ የሆኑት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ምክትል ገዢ አቶ ሰለሞን ደስታ እንደተናገሩት፤ ባንኩ የተለያዩ ተግዳሮቶችን በመሻገር በሊዝ ባገኘው ሰፊ ቦታ የዋና መስሪያ ቤት ህንጻ ግንባታ ለማከናወን የዲዛይን ሽልማት ስነስርዓት ምዕራፍ ላይ በመድረሱ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል፡፡

አቶ ሰለሞን ደስታ አክለውም የባንኩ ዋና መስሪያ ቤት ህንፃ መገንባት የህንፃ ኪራይን ለማስቀረት፤ የባንኩን ገፅታ ለመገንባት፤ ለዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር፤ ለከተማዋ ውበት ለመጨመር እና የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር ረገድ የባንኩን የፋይናንስ አቅም ለማጎልበት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ባንኩ ከዲዛይን መረጣ ባሻገር ግንባታውን በዕውቀት በመምራት በአብዛኛው በከተማችን የሚስተዋለውን የግንባታ መጓተት በማስቀረት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

እንዲሁም ከውጪ ባንኮች መምጣት ጋር ተያይዞ ባንኮች ህንፃ መገንባት ላይ ብቻ ሳይሆን የዕውቀት ሽግግር፤ የቴክኖሎጂ እና የካፒታል ግንባታ ላይ ማተኮር እንዳላባቸው በማስገንዘብ ለአሸናፊው ድርጅት እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

ከተወዳዳሪ ዲዛይኖች ኤምኤኢ ኮንሰልቲንግ አርክቴክትስ እና ኢንጂነርስ፤ ጄዲኤደብሊው ኮንሰልቲንግ አርክቴክትስ እና ኢንጂነርስ እና አዲስ መብራቱ ኮንሰልቲንግ አርክቴክትስ እና ኢንጂነርስ ከ1ኛ-3ኛ ደረጃ በመውጣት የዕውቅና ሰርተፍኬት ተሰጥቷል፡፡